አድዋ ዜሮ ዜሮ ኪሎሜትር ሙዚየም ፕሮጀክት

አድዋ_ዜሮ_ዜሮ_ኪሎ_ሜትር_ሙዚየም_ፕሮጀክት ታሪካዊ ስፍራ ነው፡፡ የአገራችን ኢትዮጵያ እምብርት ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ ይኸውም በዓለም ሕዝቦች ዘንድ አንገታችንን በኩራት ቀና አድርገን እንድንራመድ ያስቻለንን፣ የመላ ጥቁር ሕዝብ ኩራት የሆነውን አድዋ ድልየምንዘክርበት ብሎም መዲናችን አዲስ አበባን የአጠቃላይ እንቅስቃሴዎች ማእከል መሆኗን የሚያመለክት፣ እንደ አኩሪና አንጸባራቂው ድላችን ሁሉ ለምንጊዜም ጀግኖቹ ለአያት፣ ቅድመ አያቶቻችን ህያው መታወሻ በዚህ ትውልድ እየታነጸ የሚገኝ ዘመን ተሻጋሪ የግንባታ አሻራ ነው፡፡

ፕሮጀክቱ በመሃል ከተማችን ከአፄ ሚኒሊክ ሐውልት አጠገብ ከከተማ አስተዳደሩ (ማዘጋጃ ቤት) ህንጻ ፊት ለፊት የአንድ ወጣት እድሜን ለሚያህል ጊዜ ያለአንዳች ግንባታ ለዓመታት ታጥሮ በነበረ ስፍራ ላይ እየተገነባ ይገኛል፡፡

የመስቀል አደባባይ ፕሮጀክት

በታቀደለት የስምንት ወራት ግዜ ለማጠናቀቅ እቅድ የተያዘለት ይህ ፕሮጀክት ግንባታ ይበልጥ ዘመናዊ ሆኖ በመሰራት ላይ ይገኛል፡፡
አደባባዩ ቀድሞ ሲሰጣቸው የነበሩትን ሐይማኖታዊ ክብረ በዓሎች፣ ኮንሰርቶችና ልዩ ልዩ ሁነቶችን ጨምሮ ከ1,380 በላይ የመኪና ማቆሚያ እንዲኖረው ተደርጎ እየተገነባ ይገኛል፡፡ ይህን አስመልክቶም የፕሮጀክቱን ግንባታ በታቀደለት የስምንት ወር ግዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ እየተሰራ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትላልቅ ፕሮጀክቶች ግንባታ ጽህፈት ቤት ምክትል ሥራ አስኪያጅ መሬሳ ሊኪሳ (ኢንጅነር) አስታውቀዋል፡፡
ምክትል ሥራ አስኪያጁ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር በነበራቸው የግንባታው ሂደት የመስክ ምልከታ ላይ፣ የፕሮጀክት ግንባታውን በያዘለት ግዜ አጠናቆ ለአገልግሎት ለማብቃት በየደረጃው ባሉ ባለሙያዎች ሌት ተቀን እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
በአደባባዩ ቀደም ሲል በየግድግዳው ላይ ይለጠፉ የነበሩ ማስታወቂያዎችን በማስቀረት በስድስት ዘመናዊ ዲጅታል ስክሪኖች እንደሚተኩና በዋናነት የመኪና ማቆሚያ ፓርኪንግ ችግርን በከፍተኛ ደረጃ የሚቀርፍ እንዲሁም የከዚህ ቀደሙን ሐይማኖታዊ ክብረ በዓል ጨምሮ ሌሎች በርካታ ህዝባዊ አገልግሎቶችን የሚሰጥ ፕሮጀክት መሆኑን አክለው ገልፀዋል፡፡

የህዝብ ቤተ-መጽሃፍት ፕሮጀክት

በከተማው እየተሰሩ ካሉት የትላልቅ ፕሮጀክቶች ግንባታ መካከል አንዱ የሆነው የህዝብ ቤተ-መጽሃፍት ፕሮጀክት ግንባታ ሂደት እየተፋጠነ ነው።
የዚህ ፕሮጀክት ግንባታ ቫትን ጨምሮ አንድ ቢሊየን 115,977,250 ብር የተበጀተለት ትልቅ ፕሮጀክት ሲሆን የከተማው ነዋሪ በተለይ ወጣቱ ትውልድ በንባብ እራሱን እንዲያበለፅግ፣በአስተሳሰብ እንዲቀየርና ከአልባሌ ቦታዎች እንዲርቅ ሁሉን አቀፍ መሰረተ ልማት ያለውና እጅግ ዘመናዊ የሆነው ይህ ቤተ መጽሃፍት ፍጥነት ባለው ሁኔታ ግንባታው እየተካሄደ ይገኛል ፡፡
በ1.8 ሄክታር መሬት ላይ እየተገነባ ያለው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ግንባታው ሲጠናቀቅ እስከ 3500 ተገልጋዮችን ማስተናገድ የሚችል፣ 113 አውቶሞቢል ማቆም ወይም ፓርክ ማድረግ የሚያስችል ፣ የኢንፎርሜሽን ኮሚኒኬሽን ቴክኖሎጂ(ICT) እና ሌሎች አገልግሎቶችን ያካተተ የከተማው ነዋሪ ህዝብ እና ተቀማጭነታቸው በከተማዋ ለሆኑ የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ አባላት መገልገያ ትልቅ ሃብት ነው።

የከተማው ነዋሪ በተለይ ወጣቱ ትውልድ በንባብ እራሱን እንዲያበለፅግ፣በአስተሳሰብ እንዲቀየርና ከአልባሌ ቦታዎች እንዲርቅ ሁሉን አቀፍ መሰረተ ልማት ያለውና እጅግ ዘመናዊ የሆነው ይህ ቤተ መጽሃፍት፣ ከከተማው ነዋሪ በሻገር በከተማው ለሚኖሩ የተለያዩ ሀገራት ዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ አባላት አገልግሎት መስጠት የሚያስችል አቅም ያለው ነው፡፡

ሁለት አጠቃላይ የሆስፒታል ግንባታ ስራዎች

እነዜህ ስራዎች የካቲት 18ቀን 2013 ዓ.ም ተጀምረዋል። በንፋስ ስልክ ላፍቶ እና ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተሞች የሚገነቡት ሆስፒታሎቹ እያንዳንዳቸው ከ548 ሚሊዮን ብር በላይ
በጀት እንደተያዘላቸው በማስጀመሪያ ስነ ስርዓቱ ላይ ተመልክቷል። የአጠቃላይ ሆስፒታሎቹ ግንባታም በአንድ ዓመት ተኩል ጊዜ ውስጥ ይጠናቀቃል ተብሏል።
ሆስፒታሎቹ የሪፈራል አገልግሎት የሚሰጡ በመሆናቸው ከክፍለ ከተሞቹ ውጭ ከምዕራብ፣ ከደቡብ ምዕራብ እና ከምስራቅ ኦሮሚያ ለሚመጡ የህብረተሰብ ክፍሎች አገልግሎት ይሰጣሉ። የአካባቢው ማህብረሰብ የሚያነሳው የሆስፒታል አገልግሎት ተደራሽነት ችግር ለመፍታት እና ጥራቱን የጠበቀ የጤና አገልግሎት ለመስጠት ሆስፒታሎቹ ዓይነተኛ ሚና እንደሚወጡ ምክትል ከንቲባዋ ተናግረዋል።
ላለፉት ሰባት ዓመታት የሆስፒታሎቹን ግንባታ በትግእስት ለጠበቀው ህብረተሰብ ክፍል ምስጋና ያቀረቡት ምክትል ከንቲባዋ፣ ማንኛውንም ፕሮጀክት የምንጀምረው ለማጠናቀቅ ነው ብለዋል።በቅርቡ ግንባታቸው በአፋጣኝ ተጠናቆ ለአገልግሎት የበቁት የላፍቶ ገበያ ማዕከል መሰል ስራዎችን እማኝ መሆናቸውን ምክትል ከንቲባዋን ጠቀዋል።